ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ መንግስት የኦጋዴን ነፃነት ግንባር ወታደራዊ ሐላፊ አብዲ ከሪን ሼክ ሙሴን ከሶማሊያ ጋልማዱግ ግዛት አፍኖ በማገት ወደ ኢትዮጵያ መውሰዱ ተሰማ።
የኦጋዴን ነፃነት  ግንባር እንዳስታወቀው የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የወታደራዊ ጉዳዮች ሀላፊ አብዲ ከሪን ሼክ ሙሴን ጋልካዮ ከተማ ቤተሰብ ለመጎብኘት በሄደበት ወቅት በሶማሊያ የፀጥታ ሀይሎች ተይዞ ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፎ መሰጠቱን ገልጿል።
የሞቃዲሾ ነዋሪ የሆነውና የኢትዮጵያን መንግስት በጠመንጃ ከሚዋጉ ሀይሎች አንዱ የሆነው የኦጋዴን ነፃነት ግንባር ወታደራዊ ሐላፊ አብዲከሪን በጦር አውሮፕላን ተጓጉዞ ደብረ ዘይት አየር ማረፊያ መድረሱንም የዋዜማ ምንጮች ያመለክታሉ።
አብዲ ከሪን የተወሰኑ አመታትን በኤርትራ ማሳለፉንና የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት አምስት አመታት በጥብቅ ሲፈልገው የነበረ ነው።
አብዲ ከሪን ለኦጋዴን ነፃነት ግንባር ቁልፍ የሚባል ሰው ሲሆን በቅርብ አመታት የተደረጉ ወታደራዊ ዘመቻዎችን መምራቱን የድርጅቱ ምንጮች ይናገራሉ።
የሶማሊያ መንግስት አብዲ ከሪንን አሳልፎ በመስጠቱ የነፃነት ግንባሩ ማዘኑን ገልፆ የሶማሊያ መንግስት ተጠያቂ መሆን አለበት ብሏል። አብዲ ከሪን አብዛኛው ቤተሰቦቹን በጦርነት የተነጠቀ መሆኑንም ድርጅቱ ይናገራል።