ዋዜማ ራዲዮ- የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የህገመንግስት እና ፀረ-ሽብር ጉዳዮች ችሎት ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው በሚል ክስ የተመሰረተባቸውን የጥላሁን ያሚ፣ ከበደ ገመቹ፣ አብዲ አለማየሁ እና ላምሮት ከማልን መዝገብ ዛሬ ረፋድ ተሰይሞ ተመልክቷል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው ችሎት ከአንደኛ እስከ 3ኛ ያሉት ተከሳሾች ጠበቃ የማቆም አቅም እንደሌላቸው ለችሎት በመግለፅ መንግስት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው የጠየቁ ሲሆን 4ኛ ተከሳሽ የሆነችው ላምሮት ደግሞ ጠበቃ ለማቆም አቅም ቢኖራትም የሚቆምላት ጠበቃ አለማግኘቷን ገልፃ ነበር፡፡

ችሎቱም ለሁሉም ተከሳሾች የመንግስት ተከላካይ ጠበቃ እንዲቆምላቸው ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ሆኖም ዛሬ ተወክሎ የቀረበው የመንግስት ጠበቃ “የህገመንግስቱ አንቀፅ 20 ንዑስ አንቀፅ 5 እና ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ሌሎች አለም አቀፍ ስምምነቶች ጠበቃ ለማቆም አቅም የሌላቸው ተከሳሾች ፍትህ እንዳይጓደል መንግስት ጠበቃ እንደሚያቆምላቸው ይገልፃሉ እንጂ አቅም ላላቸው ሰዎች ህጉ አያዝም፡፡ የችሎት ትዕዛዝ እየነቀፍኩ ወይንም እየተቸው ሳይሆን ጠበቃ የማቆም አቅም ላላቸው ግን የመንግስት ጠበቃ ሊቆም አየይገባም፡፡ ፍትህ ተጓደለ የሚባለው አቅም ለሌላቸው ሰዎች የመንግስት ጠበቃ ካልቆመ ነው፡፡ ስለዚህ የኔ ውክልና ተገቢ ነው ብዬ ስለማላምን ትዕዛዙ ይነሳልኝ፡፡ ፍትህ እንዳይጓደል ከተፈለገ ለ50 ሰዓት ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ ጠበቆች ስላሉ ችሎቱ እሱን እንደ አማራጭ ይያዝ” ሲል አቤቱታውን አቅርቧል፡፡

የጠበቃው አቤቱታ በችሎት ከተሰማ በኋላ ላምሮት ስታለቅስ ተስተውላለች፡፡

ችሎቱ የህገመንግስቱን አንቀፅ ከግምት በማስገባት ትዕዛዝ እንደሰጠ የገለፁት ሰብሳቢ ዳኛው አንቀፁ የተቀመጠው በአጠቃላይ ፍትህ እንዳይጓደል መሆኑን በማስታወስ ጠበቃው ሁሉንም ተከሳሾች ወክለው አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

ትዕዛዙን ተከትሎ ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ላይ መቃወምያ እንደሌላቸው ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ የተጠየቁ ሲሆን ሁሉም ወንጀሉን እንዳልፈፀሙ እና ጥፋት እንደሌለባቸው ቃል ሰጥተዋል፡፡

አቃቤ ህግ በኩሉ ተከሳሾች ክደው መከራከራቸውን ተከትሎ ምስክሮቹን ለማሰማት ቀጠሮ እንዲሰጠውና አብዛኞቹ ምስክሮቹ የተከሳሾች ቤተሰቦች በመሆናቸው ፖሊስ እንዲያቀርብ እንዲታዘዝለት ችሎቱን ጠይቋል፡፡

ይሁን እንጂ ችሎቱ አቃቤ ህግ ምስክር የማስቀረብ ስልጣን ያለው መሆኑን በማስታወስ ከህዳር 23 ጀምሮ ማሰማት እንዲጀምር፤ ከአቅም በላይ ከሆነም በዕለቱ ትዕዛዝ እንደሚሰጥበት ዳኞች ገልፀዋል፡፡[ዋዜማ ራዲዮ]