airport ዋዜማ ራዲዮ- በቅርቡ የተፈቀደው ከቀረጥ ነጻ የቤት ውስጥ መገልገያ እቃወችን ኢትዮጵያውያን ማስገባት ይችላሉ ተብሎ የወጣውን ህግ ተከትሎ እቃ ባስገቡ ሰዎችና የጉምሩክ ባለስልጣን መ/ቤት መሀል ከፍተኛ ቅራኔ ተፈጠረ ።
ዜጎች ከቀረጥ ነጻ የመገልገያ ቁሳቁሶችን እንዲያስገቡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ለንግድ የማይውሉ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የግል መገልገያ እቃዎችን በሚመለከት  ታህሳስ 5 ቀን 2010 አጽድቆ ተፈጻሚ እንዲሆን ለገቢዎችና ጉምሩክ የላከው መመሪያ፤ገቢዎችና ጉምሩክ በሁሉም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ተፈጻሚ እንዲሆን አዟል።
ይህንን የመንግስት መመሪያ በመስማት በነጻ መግባት ይችላሉ ከተባሉ 321 አይነት እቃዎች ውስጥ በመንገደኞች አውሮፕላን መጫን የማይፈቀዱትን በካርጎ ያስገቡ ሰዎች ቀረጥ እንዲከፍሉ በጉምሩክ መጠየቃቸው በቦሌ የጉምሩክ ጣቢያ የተቀስቀሰው ከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞ በዚህ ሳምንት ተካሂዷል።
መንግስት ከቀረጥ ነጻ መንገደኞች እንዲያስገቡ ከተፈቀደው እቃ ውስጥ 4k በመባል የሚቆጠራው ባለ 54 ኢንች ዘመናዊ ቴሌቪዥን አንዱ ሲሆን በመምሪያው መሰረት ያስገቡ ሰዎች ለቀረጥ ከ45 እስከ 52 ሽህ ብር እንዲቀረጡ መጠየቃችን ዋዜማ ከግለሰቦቹ ሰምታለች።
መመሪያው ከወጣ በኃላ ብዙ ሰዎች የተፈቀደውን እቃ ያለቀረጥ ያስገቡ ሲሆን መመሪያው ሳይሻር ቀረጥ ክፈሉ መባሉ በዜጎች መሀከል ልዩነት የሚፈጥርና ሆን ተብሎ የተወሰኑ ሰዎችን ለመጥቀም ነው በሚልም ቦሌ ጉምሩክን አንለቅም ያሉ ሰዎች ከቀን እስከ ማታ ከስፍራው አንለቅም ማለታቸውን ዋዜማ በስፍራው በመገኘት መመልከት ችላለች።
ከቀረጥ ነጻ የተፈቀደውን መመሪያ በተመለከተ በገቢዎችና የጉምሩክ ባለስልጣን መ/ቤቶች መሀከል ግልጽ የሆነ የስራ መግባባት ባለመኖሩ የተፈጠረ ችግር መሆኑን የሚመለከታቸው ሀላፊዎች ሲናገሩ ቢደመጡም መመሪያውን አምነው እቃ ያስገቡ ሰዎች ግን መፍትሔ ማግኘት አልቻሉም ።
በመንግሥት መመሪያ መሰረት የተለያዩ እቃወችን ያስገቡ ሰዎች እቃወችቻችን ሊወረስ ነው በሚል ጩከታቸውን እያሰሙ እና የመንግስት ከፍተኛ ሀላፊዎች ጣልቃ በመግባት መግትሔ እስኪሰጡን ከመጠየቅ ውጭ መመሪያውን ሳይሻር የተጠየቅነውን ቀረጥ አንከፍልም ብለዋል ።
በአሁኑ ወቅት ከመመሪያው ውጭ ያለ አግባብ ቀረጥ እንዲከፍሉ የተጠየቁ ሰዎች ከ5 ሽህ በላይ መሆናቸውንም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለዋዜማ ገልጸዋል ። [ተጨማሪ ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ያገኛሉ]

https://youtu.be/ULnKIRpzpBc