ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮ ቴሌኮም የቀድሞ የኦፕሬሽን ክፍል ሀላፊ ኢሳያስ ዳኘው የካቲት 12 ቀን 2011 ዓም ረፋድ ላይ ቀድመው በተጠረጠሩበት ጉዳይ የዋስትና መብት በጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲሰጣቸው በተመሳሳይ ቀን ከሰዓት በኋላ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ደግሞ አቃቤ ህግ ክስ አቅርቦባቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡

በክሱም አቶ ኢሳያስ በኢትዮ ቴሌኮም የኤን.ጂ.ፒ.ኦ ዳይሬክተር በነበሩበት ወቅት የቻይና ኩባንያ ከሆነው ዜድ.ቲ.ኢ ባለቤት ጋር በጥቅም በመመሳጠር የግዢ መመርያው ከሚፈቅደው ውጪ ያለጨረታ የ44.5ሚሊየን ዶላር ውል ተፈራርመዋል የሚል ነበር፡፡
ውሉ የዩኒቨርሲቲ ኔትዎርክ ዝርጋታን የተመለከተ ሲሆን አቃቤ ህግ ተከሳሹን ከፍተኛ የሆን ጉዳት በቴሌኮሙ እና በመንግስት ላይ አድርሰዋል ብሏቸዋል፡፡ በዚህም መሰረት ስልጣናቸውን ያለ አግባብ ተጠቅመዋል ሲል የወንጀለኛ መቅጫ ህጉን አንቀፅ 407 ጠቅሶ 1ኛ ክሱን ያቀረበ ሲሆን በሁለተኛው ክሱ ላይ ደግሞ የመንግስትን ስራ በማያመች አኳኋን መርተዋል በማለት አንቀፅ 411(3) አቅርቦባቸው ነበር፡፡

ተደራርበው የቀረቡት ሁለቱም ድንጋጌዎች ታዲያ እያንዳንዳቸው ከ10 አመት በላይ በሚሆን ጽኑ እስራት እና የገንዘብ መቀጮ እንደሚኖረው በህጉ ተቀምጧል፡፡
በቀረበባቸው ክስ ላይ ዝርዝር መቃወሚያ በጠበቃቸው በኩል የካቲት 19 2011 ዓም ያቀረቡ ሲሆን አቃቤ ህግም ከሁለት ቀናት በኋላ ምላሽ ሰጥቶበታል፡፡

ጉዳዩን እያየ ያለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎትም የካቲት 29 ቀን 2011 ዓም ብይን ለመስጠት ተሰይሞ ተከሳሹ ካቀረቡት 6 የመቃወሚያ ነጠቦች አራቱን ተቀብሎ ቀሪውን ውድቅ አድርጓል፡፡

ፍርድ ቤቱ ሁለቱን የተከሳሽ የመቃወሚያ ነጥቦች ውድቅ ከማድረጉ በፊትም የተዘረዘሩት ነጥቦች ችሎቱ አሁን አቋም የሚይዝበት ሳይሆን የፍሬ ነገር ክርክር ላይ ማስረጃዎች ከቀረቡ በኋላ የሚታይ ነው በማለት ምክንያቱን አስቀምጧል፡፡

ይህ ሆኖ ሳለ በችሎቱ ተቀባይነትን ካገኙት የመቃወሚያ ሀሳቦች አንዱ ተደራራቢ ክስን በተመለከተ ነው፡፡ በዚህ ላይ የወንጀልም ሆነ የሃሳብ፣ የጊዜና የቦታ ልዩነት ሳይኖረው በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያየ የህግ አንቀፅ ስለቀረበ ሁለት ክስ ተደራርቦ ሊቀርብባቸው አይገባም በማለት ጠበቆች ተከራክረው ነበር፡፡

ችሎቱም ይህንን የመቃወሚያ ነጥብ በመቀበል የሀሳብ ልዩነት የሌለው ሁለት ክስ መቅረቡ አግባብ አይደለም ብሏል፡፡ በዚህም መሰረት አቃቤ ህግ በቀጣይ ቀጠሮ ክሱን በአንድ የህግ ድንጋጌ ስር በማጠቃለል እንዲያቀርብ ሲል ነው ትዕዛዝ የሰጠው፡፡
በሁለተኛነት ተቀባይነት ያገኘው ነጥብ የግብራበር ስም አለመጠቀሱ የህግ አግባብ የለውም የሚለው ነበር፡፡

አቃ ህግ በክሱ ካጣቀሳቸው ተጨማሪ የህግ ድንጋጌዎች መካከል አንዱ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 33ን ነው፡፡ ይህ ደግሞ በተለያዩ ሰዎች ሊፈፀም የሚችል ልዩ ወንጀል ላይ ተካፋይ መሆንን የሚያመላክት አንቀፅ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈም ከሳሽ በተደጋጋሚ በክሱ ላይ ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በማለት እንዲሁም ከዜድ.ቲ.ኢ ባለቤት ጋር እያለ በክሱ ላይ በደፈናው አስቀምጦ ነበር፡፡
ይህን ተከትሎም ተከሳሽ አቶ ኢሳያስ እና ጠበቆቻቸው ግብረ አበር ከተባለ በክሱ ሊጠቃለሉ ይገባል ስማቸውም ሊጠቀስ ይገባል ያ ካልሆነ የደምበኛችንን የመከላከል ህገ መንግስታዊ መብት የሚጋፋ ነው በማለት ተቃውመው ነበር፡፡

ችሎቱም ይህንን መቃወሚያ አግባብ ነው ብሎ የተቀበለ ሲሆን ከሳሽ አቃቤ ህግ ወንጀሉ ላይ ተሳታፊ ነበሩ ብሎ በክሱ ያስቀመጣቸውን ግብራበሮች ስም ገልፆ ክሱን አሻሽሎ እንዲያመጣ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ያ የማይሆን ከሆነ ደግሞ ድንጋጌውን አሻሽሎ እንዲያመጣ በማለት ነው ትዕዛዙ ከችሎት የተላለፈው፡፡

ሌላኛው ደግሞ በክሱ ላይ ወንጀሉ የተፈፀመበት ጊዜ አለመጠቀሱን ተከትሎ የመጣው የተከሳሽ መቃወሚያ ነው፡፡ አቃቤ ህግ አቶ ኢሳያስ የኤን.ጂ.ፒ.ኦ ዳይሬክተር በነበሩበት ወቅት ከማለተት በዘለለ ተፈፀመ የተባለው ወንጀል መቼ ወይንም በየትኛው ሰዓት እንደሆነ በክሱ አላመላከተም ነበር፡፡

የወንጀለኛ መቅጫ የስነስርዓት ህጉ ደግሞ የክስ ማመልከቻ አይነትን በሚገልፅበት በአንቀፅ 111(1)(ሐ) ስር ወንጀሉ የተፈፀመበት ጊዜና ስፍራ ተገቢ በሆነ መንገድ መገለፅ እንዳለበት ያስቀምጣል

ይህን ተከትሎም በአንድ ክስ ላይ ሊቀመጥ የሚገባ መሰረታዊ ነገር ነው ያለው ችሎቱ ከሳሽ ይህንን በቀጣይ ክሱ ላይ በማረም ጊዜውን ጠቅሶ እንዲያመጣ በማለት ትዛዝ ሰጥቷል፡፡

የመጨረሻው ነጥብ የጉዳት መጠንን የተመለከተ ሲሆን ከዚህ ጋር በተያያዘ በክሱ ላይ የ44.5 ሚሊየን ዶላር ውል ስለመፈረሙ ከመግለጽ ባለፈ በመንግስት እና በኢትዮ ቴሌኮም ላይ ደረሰ የተባለው ከፍተኛ ጉዳት መጠን አልተገለጸም፡፡

በከፍተኛ ሙስና ወንጀል ለመክሰስ እና የቀረቡትን አንቀፆች ለማጣቀስም ከፍተኛ የጉዳት መጠን ተብሎ በደፈናው መቀመጡ አግባብ አይደለም በማለት ችሎቱ የተከሳሽን መቃወሚያ ተቀብሎ አቃቤ ህግ የጉዳቱን መጠን በግልፅ እንዲያስቀምጥ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም የውል ገንዘቡ በወቅቱ በነበረው የምንዛሬ መጠን ተተምኖ እና ተስተካክሎ እንዲቀርብ ባለት አክለዋል፡፡

እነዚህን ማሻሻያዎች አቃቤ ህግ አሻሽሎ ሲያመጣ ለማየትም ለመጋቢት 9 ቀን 2011 ዓም ረፋድ ላይ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡አቶ ኢሳያስ ከላይ ክስ የተመሰረተባቸውን የዩኒቨርሲቲ ኔትዎርክ ዝርጋታ ፕሮጀክት ጨምሮ ፣ ኢትዮ ቴሌኮም በሶማሌ ክልል ባደረገው የፓወር ፕላንት ፕሮጀክት እና ያለ ጨረታ የተቀጠረ የውጪ አማካሪ ድርጅትን በሚመለከት በሙስና ተጠርጥረው ከ3 ወራት በላይ ምርመራ ሲደረግባቸው ቆይቷል፡፡

ክስ እስኪመሰረት ባለው ጊዜም በከፍተኛው ፍርድ ቤት እና እና በጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኛ ሰሚ ችሎት በተደጋጋሚ ዋስትና ሲፈቀድላቸው እና በፖሊስ ይግባኝ ሲጠየቅባቸው ነበር፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]