ዋዜማ ራዲዮ- ኢትዮጵያ ከአመታት በፊት በጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለጎረቤት አገራት ስትልከው የነበረው ችግኝ በዚህ ዓመት መቋረጡን ዋዜማ ራዲዮ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። 

መንግስት በ2013 ዓ.ም የክረምት  ወቅት ”ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ሃሳብ ተይዞ የነበረው 6 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሃ ግብር ሲያከናወን ለጎረቤት አገራት ደግሞ አንድ ቢሊዮን ችግኞችን ለማቅረብ እቅድ ይዞ ነበር፡፡

በዚህ እቅድ መሰረት ለደቡብ ሱዳን 91 ሚሊዮን፣ ለሱዳን 356 ሚሊዮን፣ ለኤርትራ 29 ሚሊዮን፣ ለጅቡቲ 9 ሚሊዮን፣ ለሶማሊያ 129 ሚሊዮን እንዲሁም ለኬኒያ 380 ሚሊዮን ችግኞችን ለማድረስ ዝግጅት መደረጉን መንግስት አስታውቆ ነበር፡፡

ይሁን እንጅ በዚሁ ዓመት ከተያዘው ዕቅድ ውስጥ መላከ የተቻለው ለኤርትራ በኦሮሚያ ክልል አማካኝነት 80 ሽህ፣ ለጂቡቲ 70 ሽህ ችግኝ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳድርና በሶማሌ ክልል አማካኝነት መላክ እንደተቻለ የአረንጓዴ አሻራ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) በቅርቡ በፓርላማ ቀርበው ተናግረው ነበር፡፡

በተጨማሪም ለፑንትላንድና ሶማሌላንድ  እያንዳንዳቸው 40 ሺህ ችግኞች የተላከ ሲሆን ወደ ኬንያና ደቡብ ሱዳን ለመላክ ታስቦ የነበረው ችግኝ በትራንሰፖርት ችግር ምክንያት ለመላክ አለመቻሉንም አብራርተዋል፡፡

ዋዜማ በ2014 ዓ.ም ለጎረቤት አገራት ለመላክ ስለተያዘው እቅድ የጠየቀቻቸው አደፍርስ በ 2013 ዓ.ም  ከነበረው አፈጻጸም በመነሳት በ2014 ዓ.ም አገር ውስጥ የሚካሄደው ተከላ ላይ ትኩረት ይደረግ በሚል ምንም አይነት እቅድ አለመያዙን ተናግረዋል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአካባቢውን አገራትም አብሮ የማልማት እቅድ ይዛ በቀጣይም ለሌሎች ጎረቤት አገራት ችግኞችን የማድረስ ስራ እንደምታከናውን የገለጸቸው ኢትዮጵያ በ2014 ዓ.ም  እንዳይላክ ያደረጉ ምክንያቶችን እንዲያብራሩ ዋዜማ የጠየቃቸው ዶ.ር አደፍርስ መልስ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በ2014 ዓ.ም በተጀመረው 4ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ- ግብር ስደስት ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]