ዋዜማ ራዲዮ- ባለፉት ሳምንታት በሀገሪቱ የዶሮና የእንቁላል ምርት ወደገበያ እንዳይገባ እገዳ የጣለው ግብርና ሚኒስቴር ስለተከሰተው ወረርሽኝ ምንነት እስካሁን የተረጋገጠ መረጃ የለውም።

ግብርና ሚንስቴር ሰኔ 3፤ 2014 ዓ.ም. ለዶሮ አርቢዎችና ላኪ ድርጅቶች በጻፈው ደብዳቤ የዶሮ በሽታ መግባቱን አረጋግጧል። ሚንስቴሩ በዚህ ደብዳቤው በተለያዩ ቦታዎች የዶሮ ሞት ክስተት እያጋጠመ መሆኑን በመጥቀስ ችግሩ ተጣርቶ መፍትሄ እስከሚሰጥበት ድረስ የዶሮና የዶሮ ውጤቶችን (ገቢና ወጪ) ላልተወሰነ ጊዜ አግዷል።

በዶሮ እርባታ የተሰማሩ ድርጅቶች የተጠቀሰውን ሕግ ተላልፈው ከተገኙ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው በዚሁ ደብዳቤ ተጠቅሷል።

በሽታው በአዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲና አየር ጤና አካባቢዎች እንዲሁም በክልል ከተሞች በቢሾፍቱና ኮምቦልቻ አካባቢ መከሰቱ ታውቋል።

የጥናት ቡድን ተቋቁሞ ናሙና በመውሰድ በሽታውን እያጠና በመሆኑን ያሳወቀው ሚንስቴሩ፤ ከአንድ ወር በኋላ ግን ግኝቱን ይፋ ማድረግ አልፈቀደም። ዋዜማ በተለይ እንቁላል ከገበያ አለመጥፋቱን ይልቁን ቀድሞ ከነበረበት ዋጋ በሦስትና አራት ብር ጨምሮ እየተሸጠ መሆኑን ጠቅሳ፤ የበሽታውን ምንነት ፣ ደረጃና ያደረሰውን ተፅዕኖ በሚመለከት የግብርና ሚንስቴርን የስራ ኃላፊዎች ብትጠይቅም  የሚኒስቴሩ ሀላፊዎች “ስለበሽታው ምንነት አላወቅንም” የሚል ምላሽ ስጥተው ዝርዝር ለመናገር ተቆጥበዋል።

በግብርና ሚንስቴር ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የዋዜማ ምንጭ እንደነገሩን የተቀሰቀሰው በሽታን ለማጥናት የ21 ቀናት ጊዜ ተሰጥቶ የነበረው ጊዜ አልቋል። በሽታው ከዚህ ቀደም የተከሰተውን አይነት “ፈንግል” አለመሆኑንና  አዲሱ በሽታው ተላላፊ መሆኑ ምንጫችን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎችና አቀናባሪዎች ማሕበርም የበሽታውን ምንነትና ስም “በተደጋጋሚ ብጠይቅም መልስ አላገኘሁም” ይላል። የመግደል አቅሙ ጠንከር ያለ በሽታ መግባቱን ግን ለዋዜማ አረጋግጧል። የማሕበሩ ስራ አስኪያጅ ብርሃኑ ሚሊዮን “ከዚህ ቀደም የተከሰቱ በሽታዎች 20 በመቶ፣ 30 በመቶ አንዳንዴም እስከ 50 በመቶ ድረስ የመግደል አቅም ነበራቸው። አሁን የተከሰተው ግን አንድ የዶሮ እርባታ ላይ ከተከሰተ ሁሉንም ዶሮዎች የመግደል አቅም አለው” ብለዋል።

በሽታው በንክኪ የሚተላለፍ መሆኑን የነገሩን ስራ አስኪያጁ አልፎ አልፎም በአየር እንደሚተላለፍ አውቀናል ብለዋል።

በሽታው ወደ ሠው ሊተላለፍ ይችላል በሚል ስጋትም የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እንደሚሰራ ማሳወቁ ይታወሳል። የኢንስቱትዩቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊ እስካሁን ከበሽታው ጋር ተያይዞ በሠው ጤና ላይ ጉዳት አለመድረሱን ለዋዜማ አረጋግጠዋል።

115 የሚሆኑ ዶሮ አርቢ ድርጅቶችን በአባልነት ያቀፈው የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎችና አቀናባሪዎች ማሕበር በሽታው አሁን ያለበት ደረጃ እየቀነሰ ነው ብሏል።

ወረርሽኙ የመግደል አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ  በተለይም አነስተኛ የዶሮ አርቢዎች ላይ ጉዳት ማድረሱ ተነግሯል። በአስር ሽህ የሚቆጠሩ ደሮዎች የሞቱባቸው አርቢዎች መኖራቸው ታውቋልም። ማሕበሩ በሽታው ካደረሰው ተፅዕኖ በላይ ክልከላው ያሳረፈው ጫና የከፋ ነው ባይ ነው። 

በሽታው ያስገደደው እግድ አርቢዎች እንቁላል ሸጠው ዶሮዎቻቸውን እንዳይመግቡ ጫና አሳድሯል ተብሏል። በተጨማሪም ከመፈልፈያ የሚወጡ ጫጩቶች ወደ እርባታ ማዕከላት እንዳይገቡ በማድረጉ ተፅዕኖ አሳርፏል። ጫቹቶች እየተደፉ መሆኑን የተናገሩት የማሕበሩ ስራ አስኪያጅ፤ ለአብነትም በአንድ የእርባታ ስፍራ ከ250 ሽህ የሚበልጡ ጫጩቶች መደፋታቸውን ተናግረዋል። 

የተፅዕኖ መጠኑን በገንዘብ ሲገልፁም “አንድ ጫጩት በ60 ብር ይሸጣል ቢባል ድርጅቱ እስከ 15 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ያስተናግዳል ማለት ነው” ብለዋል።

ዋዜማ ባገኘችው ሰነድና ግብርና ሚንስቴር ሰኔ 27፤ 2014 ዓ.ም. ለክልል መንግስታት በፃፈው ደብዳቤ እግዱን በከፊል አንስቷል። ባለ 13 ገፁ ፡የዶሮና የዶሮ ምርቶች ስርጭትና ግብይት የትግበራ መመሪያ” በዋናነት ሁለት መስፈርቶችን የያዘ ነው። ወረርሽኙ ባልተከሰተባቸው ያሉ የዶሮ እርባታ ማዕከላት የእንቁላልና የስጋ ግብይት ማድረግ እንደሚችሉ ተፈቅዷል። ይህኑም የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎችና አቀናባሪዎች ማሕበር አረጋግጧል።

ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢች ደግሞ የሚመረተው እንቁላልና ስጋ ግብርና ሚንስቴር እውቅና በሰጣቸው ባለሞያዎች የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎ ከበሽታው ነፃ መሆናቸው ከተረጋገጠ በኋላ ግብይት ማድረግ ይቻላል። [ዋዜማ ራዲዮ]