Wubalem Tadesse (PhD)

ዋዜማ ራዲዮ- በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና በማህበራዊ ፍትህ ላይ ያተኮረ የመጀመሪያውን አረንጓዴ የፖለቲካ ፓርቲ (Green Party) ለማቋቋም ጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ መሰየሙን ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

ከአስተባባሪዎቹ አንዱ ውባለም ታደሰ (ዶር) እንዳሉት የተለያዩ ታዋቂ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ምሁራን የተካተቱበት ይህ ፓርቲ በሀገሪቱ የሚታየውን ስር የሰደደ ድህነትና ማህበራዊ ፍትህ ዕጦት ለመቅረፍ አረንጓዴ ፓርቲ መፍትሄ አለው ብሎ ያምናል።

ፓርቲው ብሄርም ሆነ አካባቢ የማይገድበው ሁሉን አቀፍ መሆኑንና ለማናቸውም ኢትዮጵያውያን በሩ ክፍት መሆኑን ከአስተባባሪዎቹ ተረድተናል።

ጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴው በቅርቡ መስራች ጉባዔ እንደሚያደርግና በምርጫ ቦርድም የመመዝገብ እቅድ አለው።

አረንጓዴ ፓርቲ በታዳጊ ሀገሮች እምብዛም የተሳካለት ባይሆንም ባደጉት ሀገሮች በተለይ በጀርመን አናሳ ተፅዕኖ ፈጣሪ በመሆን ይታወቃል። ብዙውን ጊዜም ከሌሎች አውራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በማበር አጀንዳውን ያስፈፅማል። [ዋዜማ ራዲዮ]